Monday, August 17, 2009

 

ቴዲ አፍሮ ተፈታ - አንድ ብለናል። ብርቱካን ትቀጥል !

ግርማ ካሳ (muziky68@yahoo.com)
ነሐሴ 18 2001

ሰሞኑን የተፈጠረዉን ክስተት ከግምት ዉስጥ በማስገባት ኅዳር 24 ቀን 2001 ዓ.ም፣ «የቴዲ አፍሮ መታሰር በኢትዮጵያዊነት ላይ ያነጣጠረ ነዉን ?» በሚል አርዕስት ያቀረብኩትን ጽሁፍ አሻሽዬ እንደሚከተለዉ ለኢትዮጵያዊያን አንባቢያን አቅርቢያለሁ።

ከአሥራ አራት ዓመታት ስደት በኋላ አገሬን ለማየት ግንቦት ሰባት 1997 ዓ.ም. አዲስ አበባ ገባሁኝ። የታሪካዊውን ምርጫ ሁኔታ ለመከታተል ዕድል አግኝቼ ነበር። ያኔ ስለተደረገዉ ምርጫ አሁን ብዙም ማወራት አልፈልግም። ነገር ግን ከፒያሳ ወደ መገናኛ ለመሄድ ሚኒባስ ውስጥ ገብቼ ያጋጠመኝን አንድ የማልረሳዉ ክስተትት ላጫውታችሁ እፈልጋለሁኝ።

አውታንቲው “መገናኛ፣ ኮተቤ፣ …” እያለ ተሳፋሪዎችን ይጠራል። ትንሽ እንደቆየን ሚኒባሱ ይሞላና ጉዞ እንጀምራለን። ከጎኔ አንዲት ወጣት ሴት ነበረች። ትንሽ እንደሄድን እንባ በዓይኔ መፍሰስ ጀመረ። ከዚህ በፊት ሰምቼ የማላውቀው አይነት በሬጌ ቢት የቀረበና ልብን የሚሰበር ቃላት ያሉት ዜማ ሹፌሩ ያጫውት ጀመር። “ይሄ ማን ነው?” ብዬ ከጎኔ ያለችውን ወጣት ጠየቅኋት። በመገረም አይታኝ “ቴዲ አፍሮ ነዋ!” ብላ መለሰች። ብዙ ጊዜ መንፈሳዊ መዝሙሮችን ስለምሰማ ድሮ ከማውቃቸው ከእንደነ ነፃነት መለሰ - ‘አረንቻታ’ እና ከቴዎድሮስ - ‘ጉዱሮዬ’ ውጭ ብዙም የዘመኑ የኪነት ባለሞያዎችን አላውቃቸውም ነበር።

ይቅር በለውና የበደለን ወቅሰህ፣
ምህረት አስተምረን አንድ አርገን መልሰህ
ዘጸዓት ለኢትዮጵያ ወደ ተስፋ ጉዞ፣
ባህር የሚያሻግር አንድ ሙሴ ይዞ
ቅርብ ነው አይርቅም የኢትዮጵያ ትንሳዔ፣
በአንድነት ከገባን የፍቅር ሱባዔ
ፍቅር አጥተን እንጅ በረሃብ የተቀጣን፣
አፈሩ ገራገር ምድሩ መች አሳጣን
ኦሲሳ ኦሲሳ ኦሲሳ ማንዴላ፣
ይቅር አባብሎ እንዳስጣለ ቢላ
በተስፋዋ መሬት እንዲፈጸም ቃሉ፣
ሞፈሩን ያዙና ይቅር ተባባሉ …”

እያለ ነበር ቴዲ አፍሮ የሚያቀነቅነው።
ትዝ ይለኛል በምርጫው ውዝግብ ወቅት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ይህን በኔ ግምት እንደ ኢትዮጵያ የሕዝብ መዝሙር ሊቆጠር የሚገባውን ዜማ እያዜሙ ነበር የምርጫ ዘጠና ሰባት መሰረቅ ላይ ያተኮረውን ተቃውሟቸውን የገለጹት።

የዜማው መልዕክት ግልጽና ቀጥተኛ ነው። አገራችን ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብት ያደላት፣ ከማንም አገር በምንም የማትተናነስ እንደሆነች፣ እኛ ኢትዮጵያውያን የደኸየነውና የቆረቆዝነው ፍቅር በማጣታችንና ይቅር መባባል ባለመቻላችን ብቻ እንደሆነ ነው ቴዲ አፍሮ ደስ በሚያሰኝ ቃና የገለጸልን።

እርስ በርስ መገዳደል፣ እርስ በርስ መባላት አይበቃንም ወይ? ነው ያለን። እጅ ለእጃችን ከተያያዝን፣ አንድ ከሆንን፣ በዘር በኃይማኖይት ካተከፋፈልን፣ ከግል ጥቅማችን አልፈን ለወገናችን ካሰብን የኢትዮጵያ ትንሳዔ ቅርብ እንደሚሆንና እግዚአብሔር አምላክም እንደሚታረቀን ነው ያስተማረን። በዚህ ዜማ ኢትዮጵያዊነትን አይቻለሁ። ፍቅርንና መተባበርን አሽትቻለሁ።

ይህ ብቻ አይደለም። ወደ አሜሪካ ከተመለስኩኝ በኋላ አንድ ወዳጄ ቤት እራት ተጋበዝኩኝ። በርካታ ሰዎች ነበሩ። ለካ ሌላ ተመሳሳይ ዘፈን ቴዲ አፍሮ ከዚህ በፊት አውጥቶ ኖሯል፤ ቀልቤን የሳበ በቪዲዮ የተቀነባበረ ዜማ ለማዳመጥ ቻልኩ። በአቴንስ ግሪክ ኦሎምፒክ ወቅት ወገኖቻችን ያሳዩት አኩሪ ዉጤት ላይ ያተኮረና በምሳሌያዊነት የመያያዝንና የመደጋገፍን ጥቅም ለማሳየት የሞከረበት የዜማ ቅንብር ነበር።አንጋፋው ኃይሌ ገብረሥላሴ እግሩን በመታመሙ ወደ ኋላ ሲቀር፤ ቀነኒሳ እና ስለሺ ወደ ኋላ እርሱን ሲመለከቱ ነው ቪዲዮው የሚያሳየው። ወንድማቸው ወደ ኋላ በመቅረቱ ውስጣቸው አዝኖ እግራቸው ወደፊት እየሮጠ ዓይናቸው ወደ ኋላ ይመለከት ነበር።

ኃይሌ ገብረሥስላሴ፡-

“… መርቆ ሸኝቶን አገር፣ አሲዞን ሰንድቅ ዓላማ
መርዶ ነው ለወገናችን ፣ ማሸነፍ ካቃተንም
ብሰለፍ ሕመሜን ችዬ ፣ እሮጬ ላሯሩጣችሁ
ትልቁን እምነት በናንተ ፣ ጥለናል እንግዲህ አይዟቹህ …”
ሲላቸው ስለሺ እና ቀነኒሳ ደግሞ በተራቸው፦

“… እዮሃ ከባንዲራው ነው ፣ እዮሃ ቃልኪዳናችን
እዮሃ አታፍርም በኛ ፣ እዮሃ ኃይሌ አባታችን …”

እያሉ ኢትዮጵያን፤ እንዲሁም “አባታቸውን” ኃይሌን ሲያኮሩ እናያለን። አንዱ ሲደክም ሌላው እያገዘ፣ አንዱ ሲወድቅ ሌላው እየተነሳ፣ በሕብረት፣ በወንድማማችነት፣ እርስ በርስ በመተያየትና በመያያዝ አገራችንን ከውርደት ማንሳት እንደሚቻል ነው የምንማረው። የኢትዮጵያን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራ ከሌሎች አገራት ባንዲራዎች ከፍ ብላ እንድትውለበለብ ማድረግ እንደሚቻል ነው ቴዲ አፍሮ ለማሳየት የሞከረው። ምሳሌው ሩጫ ሆነ እንጂ በሁሉም መስክ ፍቅርና አንድነት ካለን ቀዳሚ የማንሆንበት ምክንያት የለም።

ከላይ የተጠቀሱት ዜማዎች ብቻ አልነበሩም።
«ስማ ስጠራህ በዚህ ማሲንቆ፣ ይጥራ ዘመኑ ሁሉም ሰዉ ታርቆ»
እንኳን አደርሰን ለአዲስ ዘመን፣ ዘመን ጀንበር ነዉ ይዉጣልን
ለዓለም ለአለም፣ እንዳይለያይለን ዘለዓለም”

ሲል ነበር ቴዎድሮስ አፍሮ በአበባየዎሽ ዜማ፣ ኢትዮጵያዉያን ከ1999 ወደ 2000 ዓ.ም በምንሸጋገርበት ጊዜ በፍቅር፣ በእርቅ በአንድነት እንድንሻገር መልካም ምኞቱን የገለጸዉ።

«ሆ በል ማሲንቆ ሆ በል ክራር ዝፈን ላገር፣
ሆ በል ዋሽንት ሆ በል ማሲኦንቆ ስታይ ሰዉ ታርቆ»

ብሎ እያቀነነቀ ነበር ፣ በአገር ዉስጥ ፣ ከአገር ዉጭ፣ በአራት ኪሎ የሚኒሊክ ቤት መንግስት ፣ በእሥር ቤት፣ በከተማ፣ በገጠርን በሚታወቅ አድራሻ ለሚኖሩ፣ የበበረሃዉና በየጫካዉ ነፍጥ አንስተዉ ለሚንቀሳቀሱ ሁሉ ተዲ አፍሮ መልእክቱን ያስተላለፈዉ።

ሰዉ ገጭተሃል በሚል ክስ፣ ቴዲ አፍሮ ወደ እሥር ቤት ከመወረዱ በፊት ደግሞ የሰማነዉ ዜማ፣ ኢትዮጵያዉያን ፊታችንን ወደ እግዚአብሄር እንድንመልስ የሚያስተምርና የሚገስጽ፣ ጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ከርስቶስ በቀራንዩ መስቀል ላይ ስለኛ የከፈለዉን የፍቅር መስዋእትነት የሚያስታወስ መንፈሳዊ ዜማ ነበር።

«አርነት አወጣኝ ቀራንዩ ላይ፣ ስለኔ ብዙ አየ ስቃይ
እዝራ በመሰንቆ ዳዊት በበገና፣ ያከበረህ አምላክ ይድርስህ ምስጋና
ዉዳሴ ለስሙ ላዳነኝ ጌታ፣ በምን ልመልሰዉ የርሱን ዉለታ
ሃሌሃሌሉያ ለታረደዉ ጌታ፣ በምን ልመልሰዉ እኔ የርሱን ዉለታ
ሰማያዊ ጸጋ የማርያም ልጅ፣ በመስቀሉ ዘጋ የሲዖል ደጅ
ባንተ ቦታ ያድርጉኝ ይስቀሉኝ ጌታዬ፣ ስቃይህን ልካፈል ባለዉለታዬ»

እያለ የመላእክት ቋንቋ በሆነው በሙዚቃ አምላኩንና አምላካችንን አከበረ። «ኢትዮጵያያ ታበጽሕ እደዊሃ አብ እግዚባሄር ሃሌሉያ። ሰላም አማን አርጋት አገራችንን » ሲል ምድርና ሰማይን የፈጠረ አምላካ የምህረት እጁን ለአገራችን እንዲዘረጋ፣ በምድራችን የእርቅ የሰላም የመዋደድ መንፈስ እንዲሰፍንም ጸለየ።

ሕግ እናስከብራለን የሚሉ ባለሥልጣናት መረጃ አለን ይላሉ። «ሰዉ ገጭቷል» የሚል ክስ አቅርበዉ ከሁለት አመት በላይ ቴዲ አፍሮ እንዲታሰር ተደረገ። የዚህ ወጣት መታሰር ብዙዎቻችንን አሳዘነ። አስቆጣም።

የስድስት አመት የእሥራት ዉሳኔ ወደ ሁለት እንዲቀየር ተደርጎ በእግዚብሄር ቸረነት ቴዲ አፍሮ የማታ ማታ ተፈታ። እኛም ተደሰትን። ቴዲ አፍሮን፣ የቴዲ አፍሮ ቤተሰቦችና ወዳጅች ሁሉ በዚህ አጋጣሚ «እንኳን ደስ ያላችሁ! እንኳን ደስ ያለን !» እላለሁኝ።

ገዢዉ ፓርቲም ለሕዝባዊ ጥያቄና ጥሪ አዎንታዊ መልስ በመስጠት፣ ብዙዎቻችን ከነበሩን በርካታ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የነበረዉ የቴዲ አፍሮ መፈታት ጉዳይ ምላሽ እንዲያገኝ በማድረጉ ምስጋና ላቀርብ እወዳለሁ። የቴዲ አፍሮ መፈታትንም አንድ ብለናል።

ነገር ግን መቀጠል ያለበት ነገር አለ። ሌላዋ የኢትዮጵያ አንድነት፣ የፍትህ፣ የሰላምና የፍቅር ሐዋርያ የሆነችዉ በአሥር ሚሊዮን በሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን ዘንድ የምትወደድ፣ ለምታምንበትና ለመርህዎቿ የቆመች፣ ከርሷ ምቾታና ድሎት ይልቅ የአገርን ጥቅም ያስቀደመች፣ አንዲት እህታችን አሁንም ኢፍትሃዊና ኢሰብዓዊ በሆነ መንገድ በቃሊቲ እሥር ቤት ትገኛለች። ይችንም ሴት ገዢዉ ፓርቲ በአስቸኳይ እንዲፈታ፣ ከሌሎች በሚሊዮን የሚቆጥሩ ወገኖቼ ጋር በመሆን አገራዊ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

ይህ ሴት ብርቱካን ሚደቅሳ ናት። ኢሕአዴግ በምርጫና ሰላማዊ በሆነ እንቅስቃሴ የሚያምን ከሆነ፣ በሌሎች ዜጎች ላይ ጥይት ተኩሳ ያልገለደችን፣ የአገሪቱን ሕገ መንግስት አክብራ የምትንቀሳቀስን፣ እንዳንዶች «ወያኔ ጠላት ነዉ። መጥፋት አለበት» በሚሉበት ጊዜ «አይደለም። ወያኔም ሆነ ማንም ኢትዮጵያዊ የማንም ሌላ ኢትዮጵያዊ ጠላት አይደለም። በፍቅር በይቅር መባባል አገራችንን በጋራና በሰላም ነዉ መገንባት ያለብን» ብላ ያስተማረችን፣ የአምስት አመት ሕጻን እናትና የሰባ አራት አመት አሮጊት እናት ጧሪን የሆነችዋን፣ ብርቱካን ሚደቅሳን መፍታት ይኖርበታል። ከሁለት አመት በፊት የነበረን ያረጀንና ያከሰመን ክስ በመምዘዝ፣ ገዢዉ ፓርቲ እየተጫወተዉ ያለዉን ጨዋታ አቁሞ ፣ ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅምን፣ በአገራችን ብሄራዊ መግባት እንዲኖር የሚረዳን ሥራ ይስራ እንላለን። ብርቱካን ሚደቅሳ አሁን ትፈታ !!!!

( ስለብርቱካን ሚደቅሳ የበለጠ ለማወቅና ይችንም ሴት ለማስፈታት የሚደረገዉን የተቀደሰ ጥረት ለማገዝ ወደ http://wwww.freebirtukan.org/ ድህረ ገጽ ሄደን መረጃዎች ማግኘት እንችላለን)

Friday, July 10, 2009

 

አቶ መለስ ብሄራዊ መግባባት አጀንዳችን ነዉ አሉ!

ግርማ ካሳ (muziky68@yahoo.com)

ሐምሌ 3 ቀን 2001
የአሥራ ሰባት አመት ወጣት ነዉ። ጥይት የጎረሰ ሽጉጥ በእጁ ይዟል። እጅግ በጣም ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት አደባባይ፣ ንግግር አድርገዉ ወደ ጨረሱ አንድ የእድሜ ባለጸጋ ሰዉ ቀስ በቀስ ይጠጋል። ሳያስቡት የያዘዉን ሽጉጥ ወደ እርሳቸዉ ደቅኖ ይተኩሳል። ሰዉዬዉ ይወድቃሉ። አካባቢዉ ተረበሸ። ተናወጠ። አምቡላንስ ተጠርቶ በአፋጣኝ በስፍራዉ ደረሰ። የወደቁትን አባት በአምቡላንሱ የነበሩ የህክምና ባለሞያዎች አነሷቸዉ። የፍጥነት ጉዞ ወደ ሆስፒታል ጀመሩ። ሆስፒታል ሳይደርሱ በመንገድ ላይ የኝህ ሰዉ ሕይወት አለፈች።

ይህ ወጣት ይጋል አሚር ይባላል። ተኩሶ የገደላቸዉም ሰዉ የቀድሞ የእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስተር ይሳቅ ራቢን ነበሩ።

ይሳቅ ራቢን እድሜ ዘመናቸዉን በሙሉ የጥይትና የመድፍ ድምጽ በመስማት ያሳለፉ ጦረኛ ወታደር ነበሩ። በፈረንጆች አቆጣጠር በ1941 ከታዋቂዉ ሞሼ ዳያን ጋር የፓልማክ ግብረኃይል አባል ሆነዉ፣ ያኔ በፍረሳንዮች ቅኝ ግዛት ስር በነበረችዉ በሊባኖስ የናዚ ጀርመን ደጋፊ የነበረዉ የፈረንሳይ ቪቺ መንግስት ወታደሮች ጋር ተዋግተዋል። በዚያ ጦርነት ጊዜ ነበር ሞሼ ዳያን አንድ አይናቸዉን ያጡት።

ከዚያ በኋላ ከአረቦች ጋር በተደረጉት ተከታታይ ጦርነቶች ትልቅ ጀግንነትና የዉትድርና ብቃት ያሳዩ፣ በእሥራኤል ታሪክ አሉ ይባሉ ከነበሩት ታላቅ የጦር መሪዎች አንዱ ነበሩ። የእሥራኤል የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የጦሩ የኢታ ማጆር ሹም ሆነውም አገልግለዋል።

ይሳቅ ራቢን «እኔ ሰላም ሳላይ እድሜዪን ጨርሻለሁ። ለልጆቻችን ሰላም ማምጣት አለብን» በሚል እምነት፣ ድፍረት የተሞላበት የሰላም እርምጃ ወሰዱ። የእሥራኤል ጠላቶች ከሚባሉ ጋር መነጋገር ጀመሩ።

ኢሳቅ ራቢን ከመገደላቸዉ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት የተናገሩት፣ ለእኛ ለኢትዮጵያዉያንና ለመሪዎቻችን ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ አስደናቂ አባባል ነበር ። «የሰላም መንገድ ከጦርነት ይሻላል። ይሄን የምለዉ እንደ አንድ ወታደር ነዉ። መከላከያ ሚኒስቴር ሆኜ የእስራኤል ወታደሮች ቤተሰቦች ስቃይ ይሰማኛል። ለነርሱ፣ ለልጆቻችን፣ ለልጅ ልጆቻችን ስንል መንግስታችን ዘላቂ ሰላም እንዲገኝ ማንኛዉንም ቀዳዳ፣ ማንኛዉንም እድል መጠቀም አለበት። ሰላም አንድ ጸሎት ብቻ አይደለም። ሰላም የጸሎታችን መጀመሪያ ነዉ» ነበር ያሉት።

የጦርነትን ፣ የጥላቻና የእልህ ፖለቲካ አደገኛነቱን ያወቁታልና፣ አብረዋቸዉ የነበሩ ጓደኞቻቸዉ ሲረግፉ፣ አካለ ስንኩል ሲሆን፣ ንብረት ሲወድም ፣ ሰዉ በሰዉ ላይ ሲጨክንና አዉሬ ሲሆን አይተዋልና፣ እርሳቸዉ የኖሩበትን በጦርነት የተበከለን አየር ለልጅ ልጆቻቸዉ ማዉረስ አልፈለጉም። እርሳቸዉ ይመኙትና ይናፍቁት የነበረዉን ሰላም፣ እርሳቸዉ ባያገኙትም እንኳን፣ የልጅ ልጆቻቸዉ እንዲያገኙ መደረግ ያለበትን ሁሉ ማድረግ እንዳለባቸዉ ተገነዘቡ። «ለልጅ ልጆቻችን ስንል ሰላም እንዲመጣ የተገኘችዋን ቀዳዳ ሁሉ መጠቀም አለብን» በሚል ጽኑ አምነት፣ በጦርነት ያልሆነ፣ የወስጥና የልብ ጀግንነት ለማሳየት ተንቀሳቀሱ። የእሥራኤል ጠላት ከተባሉት ከነያሲር አራፋት ጋር መነጋገር ጀመሩ።

ብዙ ተቃዉሞ መጣባቸዉ። እነ ናታንያሁ ተነሱባቸዉ። ግትር ፖለቲካ የሚያራምዱ፣ በጭንቅላት ሳይሆን በጠመንጃ የሚያምኑ፣ እነርሱ ብቻ ከሌላዉ እንደተሻሉ አድርገዉ በመቆጠር በትእቢት የተወጠሩ፣ ከነርሱ ዘር ዉጫ ለሌላዉ ግድ የማይሰጣቸዉ ሰዎች በርሳቸዉ ላይ ማንጎራጎር ጀመሩ።

ኢሳቅ ራቢን ግን ወደ ኋላ አላሉም። «የሰላም ጠላቶች አሉ። ሊጎዱን፣ የሰላሙን መንገድ ሊያጨናግፉን የሚፈልጉ። በድፍረት እናገራለሁ። ከፍልስጤማዉያን መካከል የወጣዉ፣ በፊት ጠላታችን የነበረዉ የፍልስጤም ነጻ አውጭ ግንባር አሁን የሰላም አጋራች ሆኗል» ሲሉ ከቀድሞ ጠላቶቻቸዉ መካከል ወዳጆችን እንዳፈሩ ተናገሩ። ከያሲር አራፋት ጋር በአንድ ላይ ለሰላም ቆሙ። ኢሳቅ ራቢን በጦርነት ሊያጠፉት ያልቻሉትን የያሲር አራፋትን ቡድን በሰላም አሸነፉት።
ታዲያ ለዘመናት በጦር ሜዳ ሲዋጉ በጥይት ያልተመቱት እኝህ ታልቅ ሰዉ፣ በሰላሙ ሜዳ በቴላቪቭ ከተማ ጥይት አገኘቻቸዉ። ለሰላም ለፍቅር ለወንድማማችነት ሲሉ ወደቁ። እጅግ ታሪካዊ፣ ተወዳጅ የሰላም ሰዉ !!!!

የይሳቅ ራቢንን ታሪክ ያለምክንያት አላመጣሁትም። አንዳንዶች ተቃዋሚዎችን መጨፍለቅ ጀግንነት ይመስለናል። አንዳንዶች ኃይልን የምንመዝነዉ በያዝነዉ ብረትና በዘረጋነዉ የሥለላ አዉታር ነዉ። መነጋገር፣ መወያየት፣ ፍቅርና መግባባት ፣ በጦርነትም ሆነ በጉልበት ከሚገኝ ጊዚያዊ መፍትሄ የበለጠ ዘለቆታ ያለዉ ጥቅም ሊያመጣ እንዲሚችል አናስብም። የሩቁን፣ እኛ ካለፍን በኋላ በልጆቻችንና በልጅ ልጆቻችን ዘመን ሊፈጠር የሚችለዉን፣ ለሁላችንም የሚበጀዉን አንመለከትም። ጊዚያዊ ጥቅማችንንና ስልጣናችን ላይ ብቻ በማተኮር ግትር ፖለቲካ እናራምዳለን።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ በፓርላም ተገኝተዉ ከተመራጮች ለቀረበላቸዉ ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ አንዲት ቀልቤን የሳበች አባባል አደመጥኩኝ።

ስለ መጪዉ የአገሪቷ ባጀት ነበር በፓርላማ ዉይይት ሲደረግ የነበረዉ። ለጦር ሰራዊቱና ለፖሊስ ከተመደበዉ ባጀት ተቀንሶ ወደ ሌላ ጠቃሚ ፕሮግራም እንዲዉል የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኅያሎች ሕብረት የፓርላማ ተጠሪ፣ አቶ ገበሩ ገብረማርያም ሃሳብ ያቀርባሉ። ፖሊስና ደህንነት አባላትን በማብዛት ብቻ የአገር ደህንነትን ለማስጠበቅ ከመሞከር ይልቅ የችግሮች ምንጭ የሆኑትን ከሥራቸዉ በንግግርና በሰላም መፍታት ቢቻል የበለጠ ለአገር ጠቀሜታ ይኖረዋል በሚል «ስለ አገር በምናስብበት ጊዜ፣ ስለ እድገት በምናስብበት ጊዜ የብሄራዊ መግባባትን የመፍጠር ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ ቢታይ ከበጀቱም ጋር ከሁሉም በላይ ጠቃሚ ነዉ» ሲሉ ሃሳባቸዉን ያቀርባሉ።

በሕብረቱ ተወካይ ለቀረበዉ ሃሳብ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሲመለሱ «ብሄራዊ መግባባት መፈጠር አለበት የሚባለዉ በራሱ ምክንያት የምንደግፈዉ አጀንዳ ነዉ። የጸጥታ አስከባሪ አቅማችንን በማሽመድመድ የሚፈጠር ብሄራዊ መግባባት ግን የለም። አገሪቱን ለዉጭ ጥቃት አጋልጦ የሚፈጠር የፖለቲካ ትርፍ የለም» አሉ።

እርግጥ ነዉ አገሪቱን ለዉጭ ጥቃት ማጋለጥ ጸረ-ኢትዮጵያዊነት ነዉ። አገሪቷ በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ምክንያት ከግብጽ ሊነሳ የሚችልን ጥቃት፣ አልሻባብ የተባለዉ በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰዉ ጨካኝ ቡድን ሊያመጣ የሚችለዉን የተወሳሰበ የሽብር አደጋ በአንድነትና በጋራ እንደ ኢትዮጵያዊ መመከት መቻል አለብን። በአዲስ አበባ ስልጣን ላይ ያለዉ መንግስት እኛ የምንወደዉ አለመሆኑ በአገራችን ላይ የመጣዉን አደጋ እንዳናይ አይኖቻችንን ሊሸፍነዉ አይገባም።

ከሰባ አመታት በፊት በቻይና፣ በማኦ ዜዱንግ የሚመራዉ የኮሚኒስት ፓርቲና በኋላ ታይዋንን በመሰረቱት በቺያንግ ካ ሼክ የሚመራዉ የናሽናሊስት ፓርቲ እርስ በርስ ይዋጉ ነበር። ጃፓን ቻይናን በምትወርበት ጊዜ ግን፣ እርስ በርስ ሲዋጉ የነበሩት ወገኖች በአንድነትና በጋራ የዉጭ ወራሪን መመከት ጀመሩ። እኛም ከቻይናዉያን ተምረን የዉስጥ ችግሮቻችንን ከዉጭ ችግሮቻችን መለየት መቻል አለብን እላለሁኝ።

ስለሆነም የአየር ኃይላችንን፣ የምድር ጦራችንን የበለጠ ማጠናከርና ማደራጀት ተገቢና እጅግ አስፈላጊ ነዉ። የአገር አንድነት፣ የአገር ደህንነት ማንም ይግዛ ማንም ቅድሚያ ሊሰጠዉ የሚገባ ጉዳይ ነዉ።

ከባጀት ጭመራዉም ባለፈም መልኩ፣ ሰራዊቱ የኢትዮጵያን ህዝብ ያንጸባረቀ፣ ከፖለቲካ ነጻ የሆነ፣ የግልሰቦችን ጥቅም ሳይሆን የአገርን ጥቅም የሚያስጠብቅ ሰራዊት እንዲሆን በተሻለ መንገድ መዋቀር ይኖርበታል። ኢትዮጵያ ጠንካራ፣ ሁላችንም የምንኮራበትና የምንተማመንበት የመከላከያ ሰራዊት ያስፈልጋታል።

እዚህ ላይ የዉጭ ጥቃት በምልበት ጊዜ ኤርትራን እንደማልጨመር እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ። ኤርትራዉያን ወንድሞቻችንና ወገኖቻችን ናቸዉ።ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ናት ብዬ ነዉ የማምነዉ። በሰላም በፍቅር እንደገና አንድ እንሆናለን የሚል ትልቅ እምነት አለኝ። ከኤርትራ ጋር የሚደረግም ጦርነት የወንድማማቾ የርስ በርስ ጦርነት እንጂ ከውጭ ኃይሎች ጋር የሚደረግ ጦርነት አይደለም።

ወደ ፖሊስና የደህንነት አባላት ስንመጣ ግን የተለየ ሃሳብ ነዉ ያለኝ። ለነርሱ በስፋት የሚጨመር ባጀት በምን መልኩ ከዉጭ አገር ከሚመጣ ጥቃት ጋር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳገናኙት አልገባኝም። አቶ ገብሩ ገብረማርያም እንዳሉት ፖሊስና ሰላዮች ከማብዛት ብሄራዊ መግባባት ላይ ማተኮሩ የበለጠ ይበጃል እላለሁ።

በፓርላማዉ በነበረዉ ክርክር ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ድርጅታቸዉ ብሄራዊ መግባባት ሊኖር እንደሚገባ ሲናገሩ ፡ «ብሄራዊ መግባባት መፈጠር አለበት የሚባለዉ በራሱ ምክንያት የምንደግፈዉ አጀንዳ ነዉ» ነበር ያሉት።

እንግዲህ ከላይ ለማሳየት የሞከርኩት የይሳቅ ራቢን ምሳሌነት እዚህ ላይ ነዉ የሚመጣዉ። እንደ ኢሳቅ ራቢን አሁን በሥልጣን ላይ ያሉት የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ከወጣትነታቸዉ ጀምሮ ጦርነትን ያዩ፣ በጦርነት የኖሩ ሰዎች ናቸዉ። በታሪክ ስለሚኖራቸዉ ቦታ፣ ስለ ልጆቻቸዉና የልጅ ልጆቻቸዉ ማሰባ አለባቸዉ እላለሁኝ።

ጸረ-ሽብርተኝነትን ለመቋቋም ተብሎ የወጣዉ አዋጅ ፣ አባቶቻችን በአድዋ በካራማራ፣ በአዲሉስ፣ በጉራ … ደማችዉን ያፈሰሱለትን አረንጓኤ ቢጫ ቀይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ሰማያዊ ኮከብ ካልተደረገበት የሚያስቀጣዉ ሕግ ፣ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የተወሰደዉ ኢሰብአዊና ኢፍትሃዊ የጭካኔ እርምጃ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በተቃዋሚውች ላይ በየወረዳዉና በየክልሉ የሚደርሰዉ ወከባ … ኢሕአዴግን ከሕዝብ ጋር የሚያጣሉ፣ ጥላቻን እንዲሰፋ የሚያደርጉ፣ ዜጎች የበለጠ ወደ ከረረ አቋም እንዲሄዱ የሚገፋፉ እንጂ ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ እንደ አጀንዳ እንደግፈዋለን ያሉትን የመግባባትንና የእርቅን መንፈስ የሚያመጡ አይደለም።

ስለሆነም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን የምለዉ ነገር ቢኖር «ድርጅትዎት በብሄራዊ መግባባት የሚያምን ከሆነ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተናገሩትን በሥራ ይተርጉሙት» የሚል ነዉ።

ጦርነት ያላወጁትን፣ በሰላምና በሕጋዊ መልኩ የሚታገሉትን፣ ከኢሕአዴግ ጋር አብረዉ ለመሥራት የተዘጋጁትን፣ አገዛዙን እንደ«ጠላት» በሚቆጥሩ ሰዎች ፊት «ወያኔ ጠላት አይደለም» ብለዉ የተሟገቱትን ማጥቃት፣ መግደል፣ ማሰር፣ ማፈን እንዴት ተደርጎ ነዉ እርቅና ብሄራዊ መግባባትን ማምጣት የሚችለዉ ? የሰለማና የፍትህ ሴት የሆኑትን ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ከስድስት ወራት በላይ በጨለማ ቤት ማሰር፣ ነገሮችን የበለጠ ያካርራል እንጂ እንዴት ተደርጎ ነዉ አገርን የሚጠቅመዉ ?

ተናዶ የኃይል እርምጃ መወሰድ፣ በበቀል መነሳሳት፣ ሰዉን ማዋረድ፣ ሰዉን መስደብ፣ ሰዉን መክሰስ በጣም ቀላል ነዉ። በአይናችን ላይ ትልቅ ምሰሶ እያለ የሌላዉን ጉዳፍ ማየት፣ የተገነባዉን ማፍረስ፣ አገርን ከድህነት ወደ ድህነት ማወረድ፣ ጠላቶችን ማፍራት፣ ሕዝብን ከሕዝብ መከፋፈል፣ ወንድምን ከወንድም ማጣላት አስቸጋሪ አይደለም።

ይሳቅ ራቢን እንዳደረጉት ጠላት የነበሩትን ወዳጅ ማድረግ፣ የፈረሰዉን መገንባት፣ አገርን ከድህነት ማውጣት፣ ችግሮችን በዉይይት መፍታት፣ የተጣሉትን ማስታረቅ፣ የተበተኑትን መሰብሰብ፣ ትችትና ወቀሳን በትህትና ተቀብሎ ስድብና አሉባልታን ደግሞ ንቆ ነገሮችን በትእግስት ማሳለፍ ግን እጅግ በጣም ከባድ ነገር ነዉ።

ስለሆነም አቶ መለስ ዜናዊንና ጓደኞቻቸዉን፣ አሁንም የቀናዉን መንገድ እንዲይዙና በፓርላማ እንደሰማነዉ ሁሉ በተግባር ለእርቅና ለብሄራዊ መግባባት መዘጋጀታቸዉን ለማሳየት ተጨባጭ ሥራዎችን ለመሥራት እንዲነሱ ጥሪ አቀርባለሁ።

ከነዚህም ከተጨባጭ ስራዎች መካከልም በቀዳሚነት፣ በዋናነትና በአስቸኳይ ትልቅ ሥራ ሊሰራበትና እልባት ማግኘት ያለበት ጉዳይ ቢኖር የወ/ት ብርቱካን እሥር ጉዳይ ነዉ።

ወ/ት ብርቱካን ቃሌ በሚለዉ ጽሁፋቸው ይቅርታ መጠየቃቸዉን በግልጽ አስቀምጠዋል።«በሽማግሌዎች የእርቅ ማግባቢያ መንፈስ መሰረት በፖለቲካ የተቀሰቀሰዉን ክስ ፖለቲካዊ እልባት ለመስጠት በማሰብ ለእርቅ ስል ከሌሎች የፓርቲዉ (ቅንጅት) መሪዎች ጋር ተስማምቼ ሰኔ 11 ቀን 1999 ዓ.ም በተጻፈዉ ሰነድ በሽማግሌዎች አማካኝነት ይቅርታ ጠይቄአለሁ። ይህ ብፈልግም ልለዉጠዉ የማልችለዉ ሐቅ ነዉ» ነበር ያሉት።

ስለሆነም አቶ መለስ ዜናዊ ለቢቢሲ ሃርድቶክ ጋዜጠኛ ለመግለጽ እንደሞከሩት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ያጭበረበሩት ወይንም ያታለሉት አንድ ነገር የለም። «የይቅርታ ዉሳኔ ለይቀር ተባዩ ከደረሰና ተቀባይነት ካገኝ በኋላ የይቀርታ ዉሳኔ በማጭበርበር ወይም በማታለል የተገኘ መሆኑ ከተረጋገጠ የይቀርታ ዉሳኔዉ ዋጋ አይኖረዉም» የሚለዉና በጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ የሚጠቀሰዉ የይቅርታ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጠር 395፣ አንቀጽ 16፣ ንኡስ አንቀጽም 2 ፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን በጭራሽ አይመለከትም። «ይቅርታ አልጠየኩም» ሳይሉ፣ የማይገናኝ ይህንን የሕግ አንቀጽ እንደ ሌጦ በመተርጎም፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች ያሏቸዉንም እኝህን የሰላም ሴት በግፍ ማሰር አሳዛኝና አሳፋሪ እንጂ በምንም አይነት መልኩ አገራዊ መግባባትን የሚፈጠር አይደለም።

ኢሕአዴጎች፣ ተቃዋሚዎች ሁላችንም ብሄራዊ መግባባትን በእዉነት ከፈለግን፣ በሁላችንም ዘንድ የልብ መሻት ካለ እንቆቅልሾቻችንን መፍተት ያችላል። ስለዚህ በትጋትና በቅንነት ወደ አንድነትና ወደ እርቅ ሁላችንም ልባችንን እናነሳሳ። ኢሕአዴግ በአስቸኳይ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በመፍታትና የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ለብሄራዊ መግባባት ያለዉን ቁርጠኝነት በግልጽ ያሳይ። እንደ ኢሳቅ ራቢን ደፋርና ሰላምን የሚያበራክቱ እርምጃዎችን ይወሰድ።


Monday, July 06, 2009

 

ብርቱካንን ከማሰር አይነት ጎጂ ድርጊት መቼ ነዉ ኢሕአዴግ የሚገደበዉ ? ከድርጅቱ ደጋፊ


ግርማ ካሳ (muziky68@yahoo.com)

ሰኔ 29 ቀን 2001

አባ መላ በሚል ስም የሚታወቁትና አፍቃሪ-ኢሕአዴግ የሲቪሊቲ ፓልቶክ ክፍልን የሚያንቀሳቅሱ የገዢዉ ፓርቲ ደጋፊ (ምናልባትም ባለሥልጣን) አንድ ከፍተኛ የኢሕአዴግ አመራር አባላትን ሲጠይቁ ከተናገሩት የሚከተልዉ ይገኝበታል።

«አንዳንድ ጊዜ ከኢሕአዴግ በኩል፣ በዳያስፖራዉ የኢሕአዴግን ደጋፊዎች ሁሉ ሳይቀሩ፣ criticise የሚያደርጉት popular ያልሆኑ ነገሮችን ትወስዳላቹህ። አላስፈላጊ የሆነ። ለምሳሌ በቅርቡ በብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የተወሰደዉ እርምጃ ምንም እንኳን ጥፋት አጥፍታለች ቢባልም ቴክኒካሊ፣ አስፈላጊ ያልሆነ confrontation ነዉ። ብዙ የምንሰራዉ፣ እንደ አገር የምንሰራዉ ብዙ ነገር አለ። በሕግ አንጻር ሁሉን ነገር እንደ ሌጦ መተርጎም የለብንም። ሌሎች moral values የሕዝብ አስተያየት የመሳሰሉ ነገሮችን ግምት ዉስጥ አስገብቶ ማየት ይገባል። የአንድ ጠንካራ መንግስት መለኪያዉ እርሱ ነዉ ብለን እናምናለን። ምን አልባት እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች፣ implication ያላቸዉን ጉዳዮች avoid ለማድረግ ኢሕአዴግ በኩል አንዳንድ ድክመት አለ። በሕዝብ ታዋቂ የሆኑ በጥሩም ሆነ በመጥፎ ተወዳጅነት ያላቸዉ የሙዚቃ ሰዉ ሊሆን ይችላል። ስፖርተኛ ሊሆን ይችላል። ወይም የፖለቲካ ሰዉ። በተለይ የብርቱካን ጉዳይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ዉስጥ እርስዎም እንደሚያወቁት፣ የሴቶች ታጋዮች ሚና በጣም በጣም ትንሽ ነዉ። በተቃዋሚም እንኳን ብትሆን «በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ እታገላለሁ» ብላ የገባች እስከሆነች ድረስ፣ በአምጽ የሚታገሉትን ተቃዉመን፣ ጠመንጃ ከሻቢያ ጋር አንስተዉ ግለሰቦችን ለመግደል፣ ተቋሞችን ለማፍረስ፣ የሚንቀሳቀሱትንም እያወገዝን፣ በሰላም «አገሬ ዉስጥ ሕግና ሕገ መንግስት አለ። መንግስትን ፊት ለፊት እታገላለሁ» ብሎ የገባዉንም ኃይል እኩል treat ማድረግ የለብንም። በተለይ ሴት በመሆኗ፣ የልጅ እናትም በመሆኗ በኢትዮጵያ ዉስጥ የሴቶችን ሚና ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ እምነት አለዉ ብዬ ስለማምን፣ ኢሕአዴግ በእንደዚህ አይነት ሰዎች ላይ የምትወስዱት እርምጃ በምንም መልክ defend ልናደርግ justify ልናደርግ እያቃተን ነዉ። ከእንደዚህ አይነት unpopular ድርጊት መቼ ነዉ ኢሕአዴግ የሚገደበዉ? ይሄን ጉዳይ በቅርቡ ለመፍታት የታሰበ ነገር አለ ወይ ?»


እኝህ ሰዉ፣ የሚደግፉት ፓርቲ ሕግን እንደሌጦ እየተረጎመ አላስፈላጊ ጎጂ ሥራዎችን እየሰራ እንደሆነ ነዉ የሚነግሩን። በተለይም በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የተወሰደዉ እርምጃ እንዳሳዘናቸዉ አበ መላ በድፍረት ገልጸዋል።

በዚች መጣጥፍ ሕግን እንደሌጦ የመተርጉሙ ጉዳይ ላይ አንዳንድ ሃሳቦች ለመስጠት እሞክራለሁ።በቅርቡ አቶ መለስ ዜናዊ ለአገር ዉስጥ ጋዜጦኞች በሰጡት ቃለ መጠይቅ ሰፋ ባለ ሁኔታ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ጉዳይ ላይ ሃተታ አቅርበዋል። ከኢሕአዴግ ደጋፊዎችና ከሌሎች፣ ወ/ት ብርቱካን ሚድቀሳ እንዲፈቱ የሚጥይቁ ብዙ ደብዳቤዎች እንደደረሳቸዉና እርሳቸዉም የወ/ት ብርቱካን መታሰር እንዳሳዘናቸዉ በቃለ መጠይቁ ወቅት ገልጸዋል።

«ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ይፈቱ» ብለዉ ከሚጠይቁት ደብዳቤዎች መካከል አንዳንዶቹ ሰብአዊነትን ከግምት ዉስጥ በማስገባት፣ ሌሎች ደግሞ «ኢሕአዴግን ይጎዳል፣ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታዉን ወደ ኋላ ይጎትታል» በሚል እንደሆነ አቶ መለስ አስረድተዉ፣ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ጉዳይ ግን የሕግ ጉዳይ በመሆኑ ምንም ማድረግ እንዳልተቻለ ነበር የተናገሩት።

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ይቅርታ ካገኙ በኋላ ይቅርታ አልጠየኩም እንዳሉ፣ ይቅርታ አልጠየኩም በማለታቸዉ ደግሞ ከዚህ በፊት ይቅርታ ሲሰጣቸዉ አጭበርብረዉ ነበር ማለት እንደሚቻል፣ በማጭበርበር የተገኘ ይቅርታ ደግሞ በሕጉ መሰረት መሰረዝ እንዳለበት ነበር አቶ መለስ የተናገሩት። ይህንን ሲናገሩ ፡

«የይቅርታ ዉሳኔ ለይቅር ተባዩ ከደረሰና ተቀባይነት ካገኘ በኋላ የይቅርታ ዉሳኔ በማጭበርበር ወይም በማታለል የተገኘ መሆኑ ከተረጋገጠ የይቅርታ ዉሳኔዉ ዋጋ አይኖረዉም

የሚለዉን የይቅርታ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 395፣ አንቀጽ 16 ፣ንኡስ አንቀጽ 2 አስበዉ እንደሆነ እገምታለሁ።

እዚህ ላይ ነዉ እንግዲህ ሁኔታዎችን ያላገናዘበ፣ የአገርን ጥቅም ከግምት ዉስጥ ያላስገባ፣ በይቅርታ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 395 ዉስጥ ያሉትን ሌሎች አንቀጾችን ሁሉ ያልተመለከተ በነጠላዉ፣ አባ መላ እንዳሉት፣ እንደሌጦ የሆነ የሕግ ትርጓሜ ነዉ የምናየዉ።በመጀመሪያ ደረጃ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ «ይቅርታ አልጠየኩም” አላሉም። ቃሌ በሚለዉ ጽሁፋቸው ለሁለተኛ ጊዜ ከመታሰራቸዉ ከአንድ ቀን በፊት፣ ይቅርታ መጠየቃቸዉን በግልጽ አስቀምጠዋል።

«በሽማግሌዎች የእርቅ ማግባቢያ መንፈስ መሰረት በፖለቲካ የተቀሰቀሰዉን ክስ ፖለቲካዊ እልባት ለመስጠት በማሰብ ለእርቅ ስል ከሌሎች የፓርቲዉ (ቅንጅት) መሪዎች ጋር ተስማምቼ ሰኔ 11 ቀን 1999 ዓ.ም በተጻፈዉ ሰነድ በሽማግሌዎች አማካኝነት ይቅርታ ጠይቄአለሁ። ይህ ብፈልግም ልለዉጠዉ የማልችለዉ ሐቅ ነዉ»


ነበር ያሉት።

በሁለተኛ ደረጃ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የተወሰደዉ እርምጃ የይቅርታ ሕጉን አላማ ያላንጸባረቀ እርምጃ ተደርጎ የሚወሰድ ነዉ። የይቅርታ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 395 አንቀጽ 11 የይቅርታው ዓላማ ምን እንደሆነ በማያሻማና በማያከራክር መልኩ በግልጽ አስቀምጦታል። አንቀጽ 11 እንዲህ ያላል ፡

“የይቅርታ አላማ የሕዝብን ደህንነትና ጥቅም ማስከበር ነዉ” ።

በአንቀጽ 11 መሰረት በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የተወሰደዉ እርምጃ ቢመዘን ምን ያህል የሕዝብን ደህንነትና የአገርን ጥቅም ያስከብራል የሚል ጥያቄን ብናነሳ የኢትዮጵያን ሁኔታ የሚከታተል ማንኛዉም ሰዉ የሚመለሰዉ ነዉ።

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉን የአገሪቱን ሕግ በመከተል፣ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እያደረጉ የነበሩ ሴት ናቸዉ። በሕግ የተመዘገበ የአንድ አብይ የፖለቲካ ፓርቲ፣ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር ናቸዉ። በ1999 ዓ.ም ማለቂያ ወቅት ከቃሊቲ እሥር ቤት ከተፈቱ ጊዜ ጀምሮ ለሁለተኛ ጊዜ እሥር ቤት እስከገበቡበት ጊዜ ድረስ የተከሰሱበት አንዳች ወንጀል የለም። የርሳቸዉ መታሰር በምንም መልኩ የአገርን ደህንነትና ጥቅም ከማስከበር አንጻር የሚያመጣዉ አዋንታዊ ድርሻ የለም።

ይልቅስ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ መታሰር ዜጎች በሰላማዊ ትግል ላይ ያላቸዉ ተስፋ እንዲሞነሙን አድርጓል። ብዙዎች ተስፋ ከመቁረጣቸዉ የተነሳ ወደ ጠመንጃ ትግል ፊታቸዉን እያዞሩ ነዉ። በኢትዮጵያዉያን ዘንድ መከፋፈሉና ጥላቻዉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሲሆን ድህነትንና እንደ አልሻባብ ያሉ ሽብርተኞችን በጋራ እንዳንመክት መተማመንና አንድነት ከመካከላችን እየጠፋ ነዉ።

«ሕግ እንደሌጦ መተርጎም ቆሞ፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በአስቸኳይ ይፈቱ። የፖለቲካ ምህዳሩን ይስፋ» እላለሁኝ። አባ መላ ያሉትን በመጥቀስ ኢሕአዴግ ከጎጂ ድርጊቶች ለራሱ፣ ለሕዝብ፣ ለአገርና ለተተኪዉ ትዉልድ ሲል እንዲቆጠብ እጠይቃለሁ።

በጋራ በፍቅር አገቻችንን አሁን ካለችበት የድህነት አዝቅት፣ የወርደት ካባ እናወጣት።


http://peacewithkinijit.tripod.com/sibhat.wma

Thursday, June 25, 2009

 

እኛም የዲሞክራሲ ጀግኖች አሉን !

ግርማ ካሳ (muziky68@yahoo.com)

















ግርማ ካሳ (muziky68@yahoo.com)

ሰኔ 29 ቀን 2001

ኔዳ አጋ ሱልጣን ትባላለች። በቅርቡ የተደረገዉን የምርጫ መጭበርበር በተመለከተ በኢራን በተደረገዉ ሰላማዊ ሰልፍ ከደህንነት አባላት በተተኮሰ ጥይት የተገደለች ናት። ከቤቷ ስትወጣ የወጣችዉ ድምጿ እንዲከበርላት፣ የሰብዓዊ መብቷ እንዲረጋገጥ በሰላም ነበር። በሕይወቷ ማከናወን የምትፈልጋቸዉ ብዙ እቅዶች ይኖሯታል። ነገር ግን እቅዶቿን ሁሉ ትታ ወደቀች። ተገደለች።

ኔዳ የዲሞክራሲ ምልክት ሆና በአለም ሁሉ ስለእርሷ እየተነገረ ነዉ። በኢራን የዲሞክራሲ ታጋዮች ዘንድ፣ በሥጋዋ ከዚህ አለም ብትለይም፣ በኢራን የዲሞክራሲ ትግል ታሪክ ዉስጥ ግን ልዩ ቦታ ይዛለች። የሞተችበት አላማም በሕዝቡ ዉስጥ ማእከል ቦታ ይዞ እየተቀጣጠለ ነዉ።

እኛ አገር ተመሳሳይ ሁኔታ ከአራት አመታት በፊት አይተናል። አሁን በሥልጣን ላይ ያለዉ የኢሕአዴግ መንግስት በምርጫ ከፍተኛ ሽንፈት ሲደርስበት፣ ኮረጆ መቀያየር ጀመረ። ሳያሸንፍ አሸንፊያለሁ ብሎ አወጀ። የምርጫዉን መጭበርበር፣ በኢራን አሁን እየተደረገ እንዳለዉ፣ ሕዝብ ሰላማዊ ሰልፍ በመዉጣት ተቃወመ። በአቶ መለስ ዜናዊ የሚመራዉ የአጋዚ ጦርና የፌደራል ፖሊሲ ትልቅ ጭካኔ የተሞላበት የኃይል እርምጃ ወሰዱ። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችን ገደሉ።

የዚያን ጊዜ ነበር የአሥራ ስድስት አመቷ ወጣት፣ የኛ «ኔዳ» የሆነችዉ፣ ሽብሬ ደሳለኝ ለዲሞክራሲና ለነጻነት ስትል የተገደለቸዉ። አለም ስለርሷ አልዘገበም። ሲኤንዔን፣ ቢቢሲ ዋሺንግተን ፖስትና ኑዮርክ ታይምስ ፎቶዎቿን አላወጡም። የምእራባዉያን አገሮች ተቃዉሟቸዉን አላሰሙም። ብዙዎች አያዉቋትም። ነገር ግን እኛ እናዉቃታለን። በኛ ዘንድ ግን የተረሳች አይደለችም።

ይሄን ጊዜ ሽብሬ ደሳለኝ ሃያ አመት ይሆናት ነበር። ምናልባትም የዮኒቨርሲቲ ተማሪ ልትሆን ትችል ነበር።

ገዳዮቿ ሊረሱ ይችላሉ። ከአራት አመት በፊት የሰሩትን ግፎች ከዚያ በኋላ እየደጋገሙ ስለፈጸሙ ብዙ ያስታዉሱታል ብዬ አላስብም። ነገር ግን አንድ የምናዉቀዉ ነገር አለ። ሽብሬ ደሳለኝ መቼም ቢሆን አትረሳም። እስከ አሁን ድረስ የሕሊና ጆሮ ላለዉ ሰዉ፣ የፈሰሰዉ ደሟ ሲጮህ ይሰማል። አሁንም ሽብሬ ደሳለኝ ትጣራለች። አሁንም መልእክቶቿ እየደረሱን ነዉ።

«ትግሉን ተቀላቀሉ። በአገራቹህ ጉዳይ ላይ ባይተዋር አትሆኑ። ከሌሎች ህዝቦች ተማሩ። ሌላዉ ሲጠቃ ዝም የሚል የፈሪ ባህልን አስወግዱ። እኛ ደማችንን ያፈሰስንበትን አላማ ከግቡ አድርሱት።» ትለናለች።

እነ በርቱካን ሚድቅሳ የሽብሬን ጥሪ ተቀብለዉ የጨካኞችን ግፍ እየተቀበሉ ነዉ። ለእዉነትና ለሐቅ በመቆም፣ ማስፈራሪያንና ዛቻን በመናቅ እርሳቸዉን ሰውተዉ ደረታቸዉን ለጥይት አሳልፈዉ ሰጥተዋል።

እኛስ ? መልሳችን ምንድን ነዉ ?

Wednesday, June 24, 2009

 

ኢትዮጵያ ጽጌሬዳችን ናት !

በግርማ ካሣ
ቺካጎ (muziky68@yahoo.com)

ኢትዮጵያን በጽጌረዳ አበባ እመስላታለሁ። ጽጌሬዳ አበባ በጣም ተወዳጅ የሆነች አበባ ናት። ብዙ ጊዜ በማስቀመጫ ዉስጥ ተደርጋ የሚመጡ እንግዶች እንዲያይዋት በሚታይ ቦታ ትቀመጣለች። የክብር የፍቅርና የዉበት ምልክት ናት። ኢትዮጵያ አገራችንም በነጻነቷና በአንድነቷ ታፍራና ተክብራ የኖረች፣ ከተለያዩ ብሄረሰቦች የተወጣጡ ልጆቿ ዉበቷ የሆኑላት፣ ለኢትዮጵያዉያን ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ህዝብ ሁሉ ኩራት የሆነች አገር ናት።

የቀድሞዉ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዘዳንት ኔልሰን ማንዴላ ሰለ ኢትዮጵይ ሲናገሩ “ኢትዮጵያ በሐሳቤ ልዩ ቦታ አላት፤ ኢትዮጵያን መጎብኘትም ፈረንሳይ እንግሊዝንና አሜሪካን ከመጎብኘት የበለጠ ይስበኛል” ይሉናል። ስለ ዳግማዊ አጼ ሚኒሊክ አንድ በተባበሩት መንግስታት ጽ/ቤት የኢኮኖሚክ ኮሚሽን ፎር አፍሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩ፣ ሴኔጋላዊ ከ አሥራ ሰባት አመታት በፊት የነገሩኝ ቁም ነገር ነበር። “ስለ አጼ ሚኒሊክና የአድዋዉ ጦርነት የሴኔጋል ተማሪዎች ይማሩታል። የአድዋዉ ድል የአፍሪካ የነጻነት ምዕራፍ ጅማሬ ነዉ። ሚኒሊክ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ አባት ናቸዉ” ሲሉ ነበር ኢትዮጵያ በሴነጋል ተወላጆች ዘንድ ያላትን ልዩ ቦታ በግልጽ ያስቀመጡልኝ። አዎ ኢትዮጵያ የኛ የኢትዮጵያዉያን ብቻ ሳይሆን የጥቁር ሕዝብ ሁሉ ጽጌሬዳ ናት።

ኢትዮጵያ እንዲህ ለጥቁር ሕዝብ ሁላ ኩራት የሆነችዉ በቀላሉ አይደለም። የኢትዮጵያን ነጻነትና ክብር ለማስጠበቅ የተከፈለዉ መስዋዕትነት እጅግ በጣም ትልቅ ነዉ።

በአድዋ፣ በማይጨዉ፣ በአዱሊስ በወልወልና በመላዉ የኢትዮጵያ ግዛት ከወራሪ ጣሊያኖች ጋር፤ በጉንደትና በጉራ ከግብጾች ጋር፤ በአፋር ምድር ከቱርኮች ጋርና እንዲሁም “ታላቋ ሶማሊያ” በሚል መርህ የተሰማራዉን የዉጭ ወራሪ ኃይል ለመመከት በሃረርጌ በተደረጉት ታላቅ ትንቅንቆች ትቅል የደም መስዋዕትነት ተከፍሏል።

በመተማ ከደርቡሾች በተተኮሰ ጥይት ያለፉትን አጼ ዮሐንስ አራተኛ፣ በመቅደላ ተራራ ለኢትዮጵያ ክብር ሲሉ እጃቸዉን ለእንግሊዞች ላለመስጠት የራሳቸዉን ጥይት የጠቱትን መይሳዉ አጼ ቴዎድሮስን ፣ የዘርዓይደረሰን፣ የአብዲሳ አጋን፣ የደጃች ባልቻ አባነፍሶን፣ የፊታዉራሪ ገበየሁን፣ የጥቁር አንበሳ ጀግኖችንና እንዲሁም በተለያዩ አጋጣሚ ለኢትዮጵይ ነጻነትና ክብር ሲሉ ህይወታቸዉን ሰዉተው ያለፉ ወገኖቻችንን ቁጠር እጅግ በጣም ብዙ ነዉ።

ጽጌሬዳ መልከ መልካምና ያማረች የሆነችዉን ያህል የሚዋጉና የሚያደሙ እሾሆችም አሏት። በአዲስ አበባ፣ በሃዉሴን፣ በአሲምባ፣ በከረን፣ በአስመራ፣ በአሶሳ፣ በጎንደር፣ በኦጋዴን፣ በምዕራብ ወለጋ፣ በበደኖ፣ በአርባ ጉጉ … በእሾህ ተወግቶ የስንቱ ኢትዮጵያዊ ደም ፈሰሰ ? ስንቱ በወንድሙ እጅ ታረደ ? የስንቱ ወጣት እናት ልጇን አጣች?


በአገራችን ለዘመናት በነበረዉ የእርስ በርስ ጦርነት ያለቁት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ተምረዉ፣ ትዳር ይዘዉ፣ ልጆች ወልደዉና ከብረዉ ለወግ ለማዕረግ መድረስ የሚችሉ ነበሩ። አሁን በሕይወት እንዳለን እንደ ማናችንም አንዳንዶቹ ሀኮሚች፣ አንዳንዶቹ መሃንዲሶች፣ አንዳንዶቹ ምሁራን፤ አንዳንዶቹ የሕግ ባለሞያዎች ሆነዉ ህብረተሰባቸዉንና አገራቸዉን ሊጠቅሙ የሚችሉ ነበሩ። ታዲይ ምን ያደርጋል የኢትዮጵያ ኋላ ቀር የደም መፋሰስና የመገዳደል ባህል ሰለባ ሆነዉ ቀሩ።

በአኩሪ ታሪካችን እንደምንኮራዉ ሁሉ በአሳፈሪዉ ታሪካችንም ማፈር አለብን እላለሁ። አገር እያለን ተሰደናል። ወገን እያለን ብቸኞች ሆነናል። ለሌሎች አገሮች የተረፈ ታላላቅ ወንዞች እያሉን ተጠምተናል። ምግብ እያለን ተረበናል። የአገራችን መሬቶች በደም ከመራሳቸዉ የተነሳ እህል ማብቀል አቁመዉ ከአመት እሰከ አመት ለህልዉናችን የፈረንጆችን እጅ እየጠበቅን ኖረናል። (ስንዴና እሩዝ ዘይትና ብስኩት እየለገሱን)

ታዲያ ለዚህ ሁሉ መከራና የሰቆቃ እሽክርክሪት ተጠያቂዉ ማን ሊሆን ይችላል ? አንዳንዶቻችን በአገራችን ለተፈጠረዉ ችግርና መከራ እጆቻችንን መንግስት ላይ እንቀስራለን። በንጉሱ ዘመን የዓጼ ሃይለስላሴ ቀዳማዊን አገዛዝ ስንረግምና ስንቃወም አብዮቱ ፈነዳ። “ኢትዮጵያ ትቅደም ያለ ምንም ደም” ተብሎ ተለፈፈብን። ወታደራዊዉ መንግስት ዙፋኑን በልጆቻችን አስክሬን ላይ ሰርቶ ገዛን። ከዚያም ቁምጣ የታጥቁ፣ “ከደርግ ብሶት የተወለድን ነን” የሚሉ “ነጻ ልናወጣችሁ፣ ዲሞክራሲ ልናመጣላችሁ ነዉ” አሉን። የከተሞቻችንን በሮች ከፍተን አስገባናቸዉ። ብዙም የተሻለ ነገር አልመጣም። አገር ወደብ አልባ ሆነች። ሃብት በጥቂቶች ተመዘበረ። ህዝብን በጎሳና በዘር ለመከፋፈል ተሞከረ። በዲሞክራሲ ስም ከአንድ በመቶ በታች የሆኑት ጨረቃ ላይ ሲመጠቁ ዘጠና ዘጠኝ በመቶ የሆነዉ ህዝባችን ቁልቁል ወረደ። ለሰላምና ለፍትህ የቆሙ ለወራት ጨለማ ቤት ይበግፍና በጭካኔ ይታሰራሉ። የፍርድ ቤት ትእዛዝ አይከበርም።

አዎን - በኢትዮጵያ ለተፈጠረዉ ችግር ዋነኛዉ ምክንያት የመልካም አስተዳደር ጉድለትና የህግ የበላይነት አለመኖር መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነዉ።

ነገር ግን በዚህ ጽሁፌ ከመንግስት ሌላ መጠየቅ ያለበት አካል እንዳለ ለማሳየት እሞክራለሁ። ይህም አካል እኔና እናንተ ነን። እያንዳንዳችን ለኢትዮጵያ አገራችን ድህነትና መቆርቆዝ በርግጥ ተጠያቂ እንደሆንን ማወቅና መቀበል ይኖርብናል። ሁላችንም መጠኑ ይለያያል እንጂ አገራችንና ወገናችንን ጎድተናል። ጥይት ላንተኩስ እንችላለን። ነገር ግን ወንድሞቻችን ሲገደሉ ዝም ማለታችን እራሱ ተጠያቂ ያደርገናል።

በአገራችን እኮ ነፍሰ ገዳይና ጨቋኝ የሚበዛዉ እኛ ስለምንፈቅድላቸዉ ነዉ። በጥቅም ይገዙላን፣ ያስፈራሩናል ከዚያ ለፍቃዳቸዉ ሕሊናችንን ሸጠን እንገዛለን። በኛ ላይ ቆመዉም በአገራችን ላይ ግፍ ይፈጽማሉ። ስለዚህ አሁን ያለዉን አገዛዝ ብቻ ከመርገም ይሄንን አገዛዝ የፈጠርነዉንና እንዲኖር ያደረግነዉን እኛኑ እርሳችንን እንውቀስ።

መተሳሰብና መደጋገፍ እንደሚያስፈልግ ለማስረዳት፡ “አሁን አንድ ኢትዮጵያዊ ጂንስ መልበስ አለበት ? ካኪ አይለብስም ። ዊስኪስ መጠጣት አለበት ? ጠጅ አይጠጣም” ብሎ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢንጂነሪንግ ፕሮፌሰር የነበረ አንድ ምሁር ከ አሥር ሶስት አመት በፊት የተናገረዉ ቁም ነገር ትዝ ይለኛል። ብልጽግና፣ ሃብትና መሻሻል መልካም ነገር ነዉ። ግን ከራሳችን አልፈን የወደቀዉን ሌላዉ ኢትዮጵያዊ ወገናችንን ለማንሳት እጆቻችን አጥረዉ ካልተዘረጉ ይህ የሞራል ዉድቀት ነዉ።

በሰሜን አሜሪካ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል። በህግ አንድ ሰራተኛ በሰዓት ከ 7$ በታች አይከፈለዉም። በጣም ዝቀተኛ ደሞዝ አገኘ ቢባል አንድ ሰዉ ቢያንስ በአመት 15000$ ያገኛል ማለት ነዉ። የካናዳ ወይንም ለአሜሪካ መንግስት ቢያንስ 15% (2500$ በአመት) ግብር ያስከፍላል። በሺህ የሚቆጠሩ የተማሩ ከ50 ፣ ከ70፣ ከ100 ሺህ በላይ የሚያገኙ ኢትዮጵያዉያን አሉ። በንግዱ ሥራ ተሰማርተዉ የከበሩና በርካታ ሱቆችና ኢንቨስትመንቶች ያሏቸዉም የሚናቁ አይደሉም።

እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በቀን አንድ ዶላር ለኢትዮጵያ ቢለይ በአመት 365 ሚሊዮን ዶላር ይደርሳል። በዚህ ገንዘብ በአየር ጠባይ መለዋወጥ በየጊዜዉ ለረሃብ የሚጋለጠዉን ወገናችንን የፈረንጆችን እጅ ሳንጠብቅ ማዳን እንችል ነበር። ታዲያ አሁንም የነጮች ጥገኛ መሆናችን መንፈሳዊ ክስረታችንን አያሳይምን? በአገራችን ላለዉ ድህነት ተጠያቂዎች አያደርገንምን ? ለካናዳና ለአሜሪካ 15% ከከፈልን ወገኖቻችንን ከረሃብ ለማዉጣትና ኢትዮጵያ በረሃብ ምሳሌነት እንዳትጠቀስ ለማድረግ ከደሞዛችን ከ 0.3 % በታች መክፈል ያቅተናል? ለልመና በጂ-20 በጂ-ስምንት ስብሰባ መጋበዝ የሚያኮራና አንበሳ የሚያሰኝ ነዉ ?

እኛ ኢትዮጵያዉያን ከቻይናዎች፤ ከጃፓኖችና ከነጮች በምን እናንሳለን ? አገራችንስ የተፈጥሮ ሃብት ከማናቸዉም ባላነሰ መልኩ እግዚአብሄር የቸራት አይደለችምን ? በአለም የተደነቁ ምሁራን፣ ሳይንቲስቶች፤ የሕግ ባለሞያዎች፣ መሃንዲሶች፣ ሃኪሞች ያሏት አገር ሆና ኢትዮጵያን ከድህነቷ ማንሳትና መቀየር እንዴት ያቅተናል?

መልሱ “አያቅተንም” ነዉ። ከቃሊቲ እሥር ቤት እንደተፈቱ አንድ ወቅት ዶ/ር በፈቃዱ ደግፌ በስዊድን ለሚገኝ የሬዲዮ ጣቢያ የተናገሩት አንድ አባባል ነበር። “ኢትዮጵያን የተቸገሩና የተጨቆኑ ከእርሷ የሚሸሹ ሳይሆን ወደ እርሷ የሚሸሹ እናደርጋታለን፤ ይቻላል” ነበር ያሉት። እዉነታቸዉን ነዉ። ኢትዮጵያን የአፍሪካ ጃፓን ማድረግ ይቻላል። የሚያስፈልገዉ አንድ ነገር ብቻ ነዉ። እርሱም ፍቅርና መተሳሰብ ነዉ።

ሐዋርያዉ ቅዱስ ጳዉሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈዉ መልእክቱ የፍቅርን ትርጉም ይሰጠናል።“ፍቅር ይታገሳል፣ ቸርነትንም ያደረጋል፤ አይቀናም አይመካም አይታበይም፤ ፍቅር የማይገባዉንም አያደረግም፣ የራሱንም አይፈልግም፤ ፍቅር አይበሳጭም በደልንም አይቆጥርም፤ ከእዉነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ሰላ አመጻ ደስ አይለዉም ..” በማለት በዝርዝር አስተምሯል።

ፍቅር ካለን አንዳችን በአንዳችን ላይ በበቀል በእልህና በጭካኔ አንነሳም። ፍቅር ካለን ያለፈዉን መጥፎ ታሪካችን ላይ ብቻ “እኝ” ብለን ልባችንን ለእርቅና ለይቅርታ አንዘጋም። ፍቅር ካለን በወንድማችን እሬሳ ላይ እየተረማመድን በደም የተገኘ ሃብት አናከማችም። ፍቅር ካለን ጎንበስ ብለን የወንድማችንን እግር እናጥባለን እንጂ በባዶ ትዕቢት አንሞላም። ፍቅር ካለን ያለችንን አንድ ዳቦ ግማሹን ቆርሰን ለተራበዉ ወንድማችን እናካፍላለን። ፍቅር ካለን በሚሊዮን የሚቆጠር ወገናችን የሰቆቃ እንባ እያለቀሰ በዳንኪራና በጨዋታ ንዋያችንን አናጠፋም። ፍቅር ካለን ያለፈን ክስ በመምዘዝ ሰላምዊ ሰዉን በጨለማ ቤት ዉስጥ በግፍና በጫካኔ አናስረም።

“ፍቅር ከወዴት ትመጣለች ?” የሚል ጥያቄ ሊጠየቅ ይችላል። መልሱ ግልጽና ቀላል ነዉ። ፍቅር የፍቅር አምላክ ከሆነዉ ከእግዚአብሄር ዘንድ ብቻ ትገኛለች። መጽሐፍ እንደሚል እግዚአብሄር እራሱ ፍቅር ነዉ።

አሜሪካኖች አገራቸዉን የመሰረቱት በእግዚአብሄር ላይ ነዉ። የሚጠቀሙበትን ገንዝብ አገላብጠን ብንመለከት እንኳን ”በእግዚአብሄር እናምናለን” የሚለዉ አረፍተ ነገር ተጽፎበታል። በእርሱ ላይ ተመስረተዋልና እግዚአብሄርም ባረካቸዉ።

እኛ ኢትዮጵያዊያን በጣም ሃይማኖተኞች ነን። ነገር ግን ሃይማኖተኝነታችን ብዙዉን ጊዜ በዉጭ ብቻ ነዉ። መንፈሳዊ አባቶቻችን በአንድ ጎን እየተራገሙና እየተወጋገዙ ሰጋ ወደሙን ይዘዉ ይቀድሳሉ። “ይህ ህዝብ በከንፈሩ ያከበረኛል ፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነዉ” ተበሎ እንደተጻፈ በከንፈራችን እንጂ በልባችን እግዚአብሄርን አልፈለግነዉም። በከንፈራችን ፍቅርን እናወራለን ልባችን ግን በጥላቻና በቂም የተሞላ ነዉ። ታዲያ እግዚአብሄር እንዴት አደርጎ ይታረቀን ?

እግዚአብሄር ሊባርከን፣ ሊያድሰንና ሊጎበኘን የታመነና ጻድቅ ነዉ። በግላችን በቤተሰባችንና በአገራችን መጀመሪያና ተቀዳሚ ካደረግነዉና “በእግዚአብሄር እናምናለን” የሚለዉን ቃል በልባችን ካተምን የፍቅር መንፈስ በምድራችን ይፈልቃል። ፍቅሩም እንድንተቃቀፍ፤ እንድንሳሳም፤ እንድነሸካከም ያደርገናል።

እኛ የአስተሳሰብ ለዉጥ ካደረግን፣ ከራሳችን ያለፉ ሥራዎችን ለመሥራት ከወሰንን፣ ከታጠርንበት ግላዊ የአስተሳሰብ መአቀፍ ከወጣን፣ በርሳችን ከተማመንን በጋራ በአንድነት መለወጥ የማንችለዉ ነበር የለም። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳንና ሌሎች የሕሊና እሥረኞችን ማስፈታት እንችላለን። በኢትዮጵያ የምንፈልገዉን የዲሞክራሲ ሥርዓት መገንባት አገራችንንም ከድህነት ማወጣት እንችላለን።

Tuesday, June 23, 2009

 

የታሰሩትስ አቶ መለስ ናቸዉ - በክፋትና በጭካኔ !

ግርማ ካሳ (muziky68@yahoo.com)


ሁለቱም በኢትዮጵያ እየተፋፈመ በመጣዉ የፖለቲካ ሂደት ዉስጥ ትልቅ ስፋራ አላቸዉ። ሁለቱም አባል የሆኑበት ደርጅት ሊቀመንበር ናቸዉ። ሁለቱም በደጋፊዎቻቸዉ ይደነቃሉ። ሁለቱም የሁለተኛ ደረጅ ተማሪ የነበሩ ጊዜ ጎበዝ ተምሪዎች ነበሩ። ሁለቱም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆነዋል። ሁለቱም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን ያጠናቀቁት በአዲስ አበባ ነዉ። ሁለቱም ወላጆች እንደመሆናቸዉ የልጅን ፍቅር ያወቃሉ። ሁለቱም ኢትዮጵያዉያን ናቸዉ።

የመጀመሪዉ አቶ መለስ ዜናዊ ይባላሉ። የአምሳ አራት አመት አዛዉንት ናቸዉ። እናታቸዉ የአዲቋላ (ኤርትራ ተወላጅ) ሲሆኑ አባታችዉ ደግሞ የአድዋ ትግራይ ሰዉ ነበሩ። ሌላኛዋ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ናቸዉ። አባታቸዉ የወለጋ ሰዉ ሲሆኑ እናታቸዉ ደግሞ የሸዋ ሰዉ ናቸዉ።

በነዚህ ሁለት የፖለቲካ ሰዎች ዉስጥ ትግራይ፣ ኤርትራ፣ ወለጋና ሸዋን እናያለን። (ከቀድሞ የኢትዮጵያ አሥራ አራቱ ክፍለ ሃገራት አራቱ ማለት ነዉ)

አቶ መለስ ወላጆቻቸዉ ያወጡላቸዉ ስም ለገሰ የሚል ነበር። «ዜናዊ» ማለት ዜና አብሳሪ ማለት ይመስለኛል። ወላጆቻቸዉ ለገሰ ዜናዊ ሲሏቸዉ «የሚያበስር ተሰጠን፣ ተወለደልን፣ ተለገሰን» ብለዉ ሳይሆን አይቀርም ብዬ አስባለሁ። መቼም ወላጆቻቸዉ ያኔ የተመኙት አቶ መለስ(ለገሰ) መልካም ብሥራት፣ መልካም ወሬ እንዲያብሰሩ ይመስለኛል።

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ስማቸዉ እንደሚገልጸዉ፣ ወላጆቻቸዉ «ያማረች፣ የጣፈጠች፣ በሰዉ የተወደደች ትሁን» ብለዉ ይመስላል ብርቱካን ያሏቸዉ። «ሚደቅሳ»ም ተመሳሳይ ትርጉም አለዉ። «ሚደቅሳ» በኦሮምኛ ማሳመር፣ ማስዋብ ማለት ነዉ።

የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳም ሆነ የአቶ መለስ ዜናዊ ቤተሰቦች ሁለቱም ልጆቻቸዉ ትልቅ ደረጃ ደርሰዉ፣ መልካም ነገር አድርገዉ፣ በመልካም ነገር ታዉቀዉ እንዲያልፉ ፍላጎት እንደነበራቸዉ ነዉ እንግዲህ የምናየዉ።

የነዚህ ሰዎች መመሳሰል እዚህ ላይ ያበቃል። አሁን ባለንበት ሁኔታ አቶ መለስ ዜናዊ ትልቅ ጭካኔ የተሞላበት ኢሰብአዊ ሥራ በሰላማዊ ዜጎች ላይ እስኪሰሩ ድረስ በጥላቻና በክፋት የተሞሉ እልኸኛ ሰዉ እንደሆኑ እያሳዩ ናቸዉ።

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ «ቅንጅት የሰዉ ጠላት የለዉም። ወያኔ ጠላት አይደለም። ለአገራችን መፍትሄ ፍቅር ነዉ። ያሰሩኝን ይቅር ብያለሁ» እስከማለት ድረስ በፍቅርና በደግነት የተሞሉ፣ የበደሏቸዉንና ወደ ሁለት አመት ገደማ በግፍ ያሰሯቸዉን ሰዎች ይቅር ያሉ ሰዉ ናቸዉ። አንድ ልዩነት በሉልኝ።

አቶ መለስ ዜናዊ በሚቆጣጠሩት የደህንነት ጽ/ቤት፣ የፌደራል ፖሊስና የአጋዚ ጦር ይመካሉ። እነዚህን ሕሊና የለሽ ሰዎች በመላክ በመቶ የሚቆጠሩ ዜጎችን በጠራራ ጸሃይ አስገድለዋል። በመቶ ሾህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን በግፍ አሳስረዋል። ሰላማዊ መንደሮችን እንዲቃጠሉ አስደርገዋል።
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የታጠቀ ሰራዊት የላቸዉም። በቤታቸዉ መሳሪያ አልተገኘም። በእጆቻቸዉ የወደቀዉን ያነሳሉ እንጂ የቆመዉን ተኩሰዉ አይጥሉም። የሚተማመኑት በሕዝብ ጉልበት እንጂ በጠመንጃ አይደለም። ሁለተኛ ልዩነት በሉልኝ።

አቶ መለስ ዜናዊ በተደጋጋሚ እርሳቸዉንና ደጋፊዎቻቸዉን ትዝብት ዉስጥ እስኪከቱ ድረስ የሚዋሹ ቀጣፊ ሰዉ ናቸዉ። ለምስሌ የቅንጅት መሪዎች ከሁለት አመታት በፊት በተፈቱ ጊዜ አቶ መለስ « ከአሁን በኋላ ወደ ፊት እንጂ ወደ ኋላ መመለስ የለብንም። ሕግን እስካልጣሱ ድረስ (የተፈቱት እሥረኞች) ሙሉ የፖለቲካ መብታቸዉ ተጠብቆ መንቀሳቀስ ይችላሉ» ነበር ያሉት። ነገር ግን ታሪካቸዉን ለዉጠዉ፣ ቀድሞ ከተፈቱት እሥረኞች መካከል ወ/ት ብርትካን ሚደቅሳ በግፍ እንድትታሰር ፈቅደዋል።

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ያላደረጉትን «አድርጊያለሁ» እንዲሉ፣ እንዲዋሹ ግፊትና ዛቻ ቢደረግባቸዉም «እምቢ» ብለዉ ለእዉነት የቆሙ ሰዉ ናቸዉ። ለእዉነትም በመቆማቸዉ ትልቅ ዋጋ በአሁኑ ወቅት በመክፈል ላይ ይገኛሉ። ሶስተኛ ልዩነት በሉልኝ”አቶ መለስ ዜናዊ ከቀድሞ የ66ቱ አብዮት ዘመን ከነበረዉ፣ እርስ በርስ በደም ከተቃባዉ ፣ እምነተ ቢስ ፍልስፍናን ለኢትዮጵያ ህዝብ ካስተዋወቀዉ፣ አገራችንን ወደ ጨለማ ከወሰደዉ ትዉልድ ናቸዉ። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በጥላቻና በቂም በቀል ካልተሞላዉ ከአዲሱ ትዉልድ ናቸዉ። አራተኛ ልዩነት በሉልኝ !

ምንም ቢሆን ክፉ የሰራ ሰዉ በመንፈሱ ሰላም ስለማያገኝ ፣ አቶ መለስ ዜናዊ የጭንቀትና የመንፈስ ረብሻ፣ የፍርሃት እሥረኛ ሆነዉ እየተሰቃዩ ናቸዉ። እራሳቸውን ይፈራሉ። አብረዋቸዉ ያሉትን የፖሊት ቢሮ አባላት ይፈራሉ። ህዝቡን ይፈራሉ። (ምናልባት የማይፈሩት ጎርደን ብራዉንና ሲልቪዮ ቤሎስኮኒን ብቻ ሳይሆን አይቀርም።) ሌሊት፣ በቤተ መንግስትም በላጠጠ መኝታ ላይ እየተኙ እንቅልፍ የላቸዉም። ለዚህ ሳይሆን አይቀርም ነገሮችን ለመርሳት ያስችል ዘንድ ሲጋራና ጫት አረቄና ካቲካላ የአራት ኪሎን ቤተ መንግስት የሞላዉ። አላወቁትም እንጂ የታሰሩትስ አቶ መለስ ዜናዊ እራሳቸዉ ናቸዉ ። በክፋትና በጭካኔ !

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በመንፈሳቸዉ ነጻ የሆኑ ሴት ናቸዉ። በሥጋ በማይመች ቦታ ታስረዋል። ግን በዚያ በማይመች ቦታ ሆነው የጣፈጠ እንቅልፍ ይተኛሉ። ዉስጣቸዉ በፍርሃት የተሞላ አይደለም። በራሳቸዉ ይተማመናሉ። ከማንም ጋር መኖር ይችላሉ። በየትም ቦታ ቢሄዱ ማንም አይነካቸዉ።አምስተኛ ልዩነት በሉልኝ!

እግዚአብሄር አቶ መለስን ከመነፈሳዊ እሥራት ወ/ት ብርቱካን ሚድቅሳ ደግሞ ከሥጋ እሥራት ይፍታቸዉ !

Friday, June 19, 2009

 

አቶ ስብሐት ነጋ በብርቱካን መታሰር ላይ

ሰኔ 12 ቀን 2001

የዘመኑ ቴክሎሎጂ ከፈጠራቸዉ የመገናኛና የመወያያ መድረኮች አንዱ ፓልቶክ ነዉ። በኢትዮጵያዉያን የሚንቀሳቀሱ በርጋታ ፓልቶክ ክፍሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዙ ነዉ። ከነዚህ ፓልቶክ ክፍሎች መካከል የኢትዮ ሲቪሊቲ ፓልቶክ ክፍል አንዱ ነው። ይህ ክፍል ከሌሎች ክፍሎች የሚለየዉ ነገር ቢኖር 95 በመቶ አፍቃሪ ኢሕአዴጎችን ያሰባሰበ መሁኑ ነዉ። የክፍሉ አስተባባሪዎች ጠንካራ የገዢዉ ፓርቲ ደጋፊዎች ምናልባትም በሥርዓቱ ዉስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸዉም ሊሆኑም ይችላሉ። በተለያዩ መጣጥፍት ለኢሕአዴግ አባላት፣ ፓርቲያቸዉ ከሕዝብ እንዲታረቅና ወደ ቀናዉ መንገድ እንዲመለስ ቀርቦላቸዋል። ከነርሱ ዉስጥ ጥሩ ልብ ያላቸዉ ሰዎች አይለዉ ወጥተዉ መልካም ነገር ሊፈጠር ይችላል የሚል ትንሽ ብትሆንና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየመነመነች ብትመጣም ተስፋ ያለን ጥቂት አይደለንም።

በዚህ መንፈስ የኢሕአዴግ ደጋፊዎችን ለማነጋገር፣ ዉስጥ ዉስጡን ትልቅ ግፊት ማድረግ እንዳለባቸዉ ለማሳሰብ ወደዚህ የሲቪሊቲ አፍቃሪ ኢሕአዴግ ፓልቶክ ክፍል ገባሁ። በኔና በሚሊዮን በሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን ዘንድ ትልቁና አንገብጋቢ ጉዳይ የሆነዉን በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ እየተፈጸመ ያለዉን ኢሰብዓዊና ኢፍትሃዊ ግፍን በተመለከተ ሕሊና ያለዉ ሰዉ በሙሉ፣ ኢሕአዴግን እንደግፋለን የሚሉ ሳይቀር ድምጻቸዉን ማሰማት እንዳለባቸዉ አሳሰብኩኝ።
በክፍሉ ያሉ በርካታ የኢሕአዴግ ደጋፊዎች የወ/ት ብርቱካን መታሰር እንዳሳዘናቸዉና አጥብቀዉ እንደተቃወሙት፣ ለአመራር አባላቱም በግልጽ ያላቸዉን ትልቅ ተቃዉሞ እንዳቀረቡ ፣ ወደፊት ወ/ት ብርቱካን እንድትፈታ ጥረታቸዉ እንደሚቀጥሉ አሳወቁኝ። ምሳሌም እንዲሆን አቶ ስብሀት ነጋ በክፍሉ ቀርበዉ ቃለ መጠይቅ በተደረገላቸዉ ጊዜ በጣም ጠንካራ በሆነ መልኩ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ጉዳይ እንደተነሳ ነገሩኝ። ቃለ መጠይቁን እንዳዳምጥ የኢንተርኔት አድራሻዉን አሳወቁኝ።

ጊዜም አልፈጀብኝም ከአቶ ስብሀት ነጋ ጋር የተደረገዉን ረጅም ቃለ መጠይቅ አዳመጥኩኝ። በቃለ መጠይቁ አብዛኛዉ በአሜሪካን ድምጻ ሬዲዪ አቶ ስብሀት ከተናገሩት ይልተለየ ነበር። ሕግ የበላይ መሆን እንዳለበት፣ ሐገ መንግስቱ መከበር እንዳለበት፣ ሕገ መንግስቱ እንደብርቅዬ ልንጠብቀዉ የሚገባ እንደሆነ አቶ ስብሀት አጠንክረዉ ተናገሩ። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በተመለከተ አባ መላ በሚል ስያሜ የሚታወቀዉ የክፍሉ ዋና አስተባባሪ የሚከተለዉን ጥያቄ አቀረበ። «አንዳንድ ጊዜ ከኢሕአዴግ በኩል፣ በዳያስፖራዉ የኢሕአዴግን ደጋፊዎች ሁሉ ሳይቀሩ፣ criticise የሚያደርጉት popular ያልሆኑ ነገሮችን ትወስዳላቹህ። አላስፈላጊ የሆነ። ለምሳሌ በቅርቡ በብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የተወሰደዉ እርምጃ ምንም እንኳን ጥፋት አጥፍታለች ቢባልም ቴክኒካሊ፣ አስፈላጊ ያልሆነ confrontation ነዉ። ብዙ የምንሰራዉ፣ እንደ አገር የምንሰራዉ ብዙ ነገር አለ። በሕግ አንጻር ሁሉን ነገር እንደ ሌጦ መተርጎም የለብንም። ሌሎች moral values የሕዝብ አስተያየት የመሳሰሉ ነገሮችን ግምት ዉስጥ አስገብቶ ማየት ይገባል። የአንድ ጠንካራ መንግስት መለኪያዉ እርሱ ነዉ ብለን እናምናለን። ምን አልባት እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች፣ implication ያላቸዉን ጉዳዮች avoid ለማድረግ ኢሕአዴግ በኩል አንዳንድ ድክመት አለ። በሕዝብ ታዋቂ የሆኑ በጥሩም ሆነ በመጥፎ ተወዳጅነት ያላቸዉ የሙዚቃ ሰዉ ሊሆን ይችላል። ስፖርተኛ ሊሆን ይችላል። ወይም የፖለቲካ ሰዉ። በተለይ የብርቱካን ጉዳይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ዉስጥ እርስዎም እንደሚያወቁት፣ የሴቶች ታጋዮች ሚና በጣም በጣም ትንሽ ነዉ። በተቃዋሚም እንኳን ብትሆን «በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ እታገላለሁ» ብላ የገባች እስከሆነች ድረስ፣ በአምጽ የሚታገሉትን ተቃዉመን፣ ጠመንጃ ከሻቢያ ጋር አንስተዉ ግለሰቦችን ለመግደል፣ ተቋሞችን ለማፍረስ፣ የሚንቀሳቀሱትንም እያወገዝን፣ በሰላም «አገሬ ዉስጥ ሕግና ሕገ መንግስት አለ። መንግስትን ፊት ለፊት እታገላለሁ» ብሎ የገባዉንም ኃይል እኩል treat ማድረግ የለብንም። በተለይ ሴት በመሆኗ፣ የልጅ እናትም በመሆኗ በኢትዮጵያ ዉስጥ የሴቶችን ሚና ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ እምነት አለዉ ብዬ ስለማምን፣ ኢሕአዴግ በእንደዚህ አይነት ሰዎች ላይ የምትወስዱት እርምጃ በምንም መልክ defend ልናደርግ justify ልናደርግ እያቃተን ነዉ። ከእንደዚህ አይነት unpopular ድርጊት መቼ ነዉ ኢሕአዴግ የሚገደበዉ? ይሄን ጉዳይ በቅርቡ ለመፍታት የታሰበ ነገር አለ ወይ ?»

እዚህ ላይ አባ መላ ለመናገር እንደሞከረዉ ገዢዉ ፓርቲ በወ/ት ብርቱካን ላይ የወሰደዉ እርምጃ በምንም መልኩ ሚዛን የማይደፋ፣ የራሳቸዉን ደጋፊዎች እንኳን ማሳመን ያልቻለ ትልቅ ስህተት እንደሆነ እናያለን።

በመርህ ደረጃ ማንም ሰዉ ለሕግ መገዛት እንዳለበትና ከሕግ በላይ ሊሆን እንደማይችል አቶ ስብሃት ከተናገሩ በኋላ የሚከተለዉን ነበር ያሉት፡

«ማንኛዉ እርምጃ ሲወሰድ በጥልቀት የማንኛዉም እርምጃ መነሻዉና መድረሻው ጠቃሚነቱና ጉዳቱ መታወቅ አለበት። ማንኛዉም እርምጃ ጉዳት የሌለዉ የለም። እኔ ወደ ቤቴ ከዚህ ስሄድ risk አለዉ። ግን አልሄድም ልል አልችልም። መሄድ አለብኝ። ስለዚህ risk የሌለዉ ነገር የለም።ጉዳቱን ጥቅሙ የትኛዉ ይበለጣል ነዉ። ብርቱክንን ማሰር ጉዳት አለዉ። ጥቅሙስ ? ጉዳቱና ጥቁምን ማስረዳት አለመቻላችን፣ አለማስተማራችን፣ አለማሳወቃችን፣ ከመደረጉ በፊትም ከተደረገም በኋላም ጉድለታችን ይመስለኛል። ከዚህ ባሻገር «አሁን ምን እየታሰበ ነዉ» ላልለከዉ እኔ በአገር ጥቅም ላይ compromise እርቅ መምጣት የለበትም። ማንኛዉም ሰዉ ከጥፋቱ በላይ መቀጣት የለበትም። ከጥፋቱ በታችም መቀጣት የለበትም። የፈጸመዉን ቅጣት የሚመጥን ቅጣት ማግኘት አለበት። ስለዚህ ብርቱክናም የፈጸመችዉን ጉዳት የሚመጥን ቅጣት ማግኘት አለባት። ከዚያ በታች ሳይሆን ከዚያ በላይ ሳይሆን። ምንድን ነዉ ጥፍቷ ? ከሰላም ጋር የተያያዘ ነዉ ? ምንድን ነዉ የተከሰሰችበት አንቀጽ ? አላዉቀዉም ! አንቀጹ ምን ያስቀጣል ? አላዉቀዉም። ግን ፍትሃዊና ቀልጣፋ ፍርድ ግን እንድታገኝ እመኝላታለሁ።»

እዚህ ላይ አቶ ስብሀት «ብርቱካን የተከሰሰችበትን ጥፋት አላዉቀዉም» ነዉ የሚሉን። አቶ ስብሀት ብርቱካን ለምን እንደታሰረች ያጡታል ብዬ አላምንም። ነገር ግን ወ/ት ብርቱካን ላይ የደረሰዉ ግፍ አተፋች የተባለዉን በጭራሽ የሚመጥን እንዳልሆነ፣ አተፋች የተባለዉም በሕግ ፊት ሚዛን የሚደፋ እንዳልሆነ የተረዱና የሚያምኑ ይመስለኛል። በዚህም ምክንያት እንደ ኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራር አባል እነ በረከት የሚመልሱትን መልስ ለመመለስ የከበዳቸዉና እንዲሁ በደፈናዉ «አላዉቅም» ብለዉ ማለፉን የመረጡ ይመስላል።

ከአንዳንድ ምንጮች ለመረዳት እንደተቻለዉ በኢሕአዴግ ዉስጥ በጣም አክራሪና ግትር ከሚባሉት መካከል አቶ ስብሀት ነጋ አንዱ ናቸዉ። እኝህ ሰዉ ከሁለት አመታት በፊት የቅንጅት መሪዎች መፈታት የለባቸዉ የሚል ጠንክራ አቋም የነበራቸዉ ሲሆን ለረጅም ዘመን የድርጅቱ መሪ እንደመሆናቸዉ ከበስተጀርባ ሆነዉ እንደ ቀድሞ የጣሊያን ማፊያ መሪዎች ብዙ ነገሮችን የሚያሽከረክሩ ናቸዉ የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም። ከዚህ በፊት ባደረጉት ቃለ መጠይቅ «ቅንጅት ጠላት ነዉ» የሚል አሳፋሪና አሳዝኝ አባባል መጠቀማቸዉም ይታወሳል።

ኦዲዮዉንም ለማዳመጥ ከታች ያለዉ የኢንተርኔት አድራሻ ጋር ይሂዱ !

http://peacewithkinijit.tripod.com/sibhat.wma

This page is powered by Blogger. Isn't yours?